የሥነምግባርና ጸረ-ሙስና ሥልጠና ተሰጠ
የድርጅቱ የሥነምግባርና ጸረ-ሙስና መምሪያ ከፌዴራል ሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ጥር 28-29/2017 ዓ.ም ያዘጋጀው ሥልጠና ለድርጅቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣የዴፖ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ለቡድን መሪዎች ተሰጠ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እስመለዓለም ምህረቱ ባስተላለፉት መልዕክት ሥልጠናው መንግሥት ከሙስና የጸዳች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የያዘው አቅጣጫ ስለመሆኑ፣ በሥልጠናው ላይ የተሳተፉ አካላት ከሥልጠናው የሚገኘውን ግብዓት በመጠቀም መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ከሙስና የጸዳች ኢትዮጵያ ለመፍጠር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አደራ በማለት ሥልጠናውን ዶ/ር ዮሐንስ ጴጥሮስን ለመስጠት ስለተገኙ አመስግነው ስልጠና ፕሮግራሙን ከፍተዋል።
ሥነምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልዕኮ ስኬት በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የጸረ-ሙስና አዋጅን፣ የሙስና ዓይነቶችና ባህሪያቸውን፣ በዘርፉ የሚሰተዋሉ የሙስና ወንጀሎችን በመለየት መከላከል የሚቻልባቸው ስልቶች ዙሪያ ግንዛቤ የፈጠረ ስልጠና ተሰጥቷል።
ሙስና የአገርን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብሮችን የሚጎዳ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ መከላከል ያለበት ስለመሆኑ፣ በአንድ ተቋም፣ በአንድ መምሪያ ወይም በአንድ ኃላፊ ብቻ መከላከል የማይቻል ስለሆነ የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚፈልግ ተገልጿል። ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን በማጠናከር ሙስና ለአገር ዕድገት ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ማድረስ እንደሚቻል መረዳት ተችሏል።
የድርጅቱን አሰራር፣ መመሪያ ደንብ፣ የሥራ ሂደትን ግልጽ በማድረግ ሙስናን መከላከል እንደሚቻል የተገለጸ ሲሆን ግልጽ ያልሆኑትን አሰራሮች ካሉ በመፈተሽ ማስተካከል አስፈላጊ ስለመሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል።