አጠቃላይ በነዳጅ ሥራዎች ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እና በናይል ፔትሮሊየም ካምፓኒ መካከል ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም አጠቃላይ በነዳጅ ሥራዎች ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እስመለዓለም ምህረቱ በፊርማ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ቀደም ሲል ለረጅም አመታት ከናይል ፔትሮሊየም ካምፓኒ ጋር ሲሰራ እንደነበር ገልጸው ይህ ዛሬ የተፈረመው ስምምነት አጋርነታቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑንና የሁለቱንም ድርጅቶች ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ አብራርተዋል፡፡ ድርጅቱ ከሱዳን ፔትሮሊያም ኮርፖሬሽን ቤንዚን ሲያቀርብ በነበረበት ወቅት የጭነት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ ሚና ሲጫወት እንደነበር ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ LPG ከሱዳን ፔትሮሊያም ኮርፖሬሽን ለመግዛት ድርጅቱ የነበረውን ውል በማደስ ሥራውን ለመቀጠል ምቹ ሁኔታ መኖሩንም ጠቅሰው ናይል ፔትሮሊየም ካምፓኒ ከድርጅቱ ነዳጅ እየገዛ በማደያው በኩል ለህብረተሰባችን ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ናይል ፔትሮሊየም ካምፓኒ ቤንዚን ከኢታኖል ጋር የመቀላቀል ሥራ በማከናወን ውጤታማ ሥራ ሲሰራ መቆየቱንም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገልጸዋል።

ናይል ፔትሮሊየም ካምፓኒ የሱዳን ኃላፊ ሚስተር ኦሱማን ኤል አሚን ሙስጠፋ ሞሐመድ በበኩላቸው የሁለቱ ድርጅቶች ታሪካዊ አጋሪነት ወደ ላቀ ደረጃ ከማሸጋገር አንጻር የመግባቢያ ስምምነቱ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፤ በነዳጅ ኢንዱስትሪ ዙሪያ ከፍተኛ ልምድ ያለው ስለመሆኑ አብራርተዋል።

ናይል ፔትሮሊየም ካምፓኒ ነዳጅ በማደያ በኩል ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ፣ ኢታኖልን ከቤንዚን ጋር መቀላቀል፣ የLPG አቅርቦት፣ ወዘተ ዙሪያ ከፍተኛ ልምድ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

LPG ለማገዶ አገልግሎት ጥቅም ላይ የሚውል የነዳጅ ምርት ስለሆነ ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የደን ጭፍጨፋ ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ድርጅቱ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish
Scroll to Top
Scroll to Top